Online Mezmur  Your Online Mezmur Lyrics 

 

Psa 147:7: Sing to the LORD with thanksgiving; Sing praises on the harp to our God,

Show Version Name:      Bible Cross Reference        Who We Are In Christ        Bible Verses by Topic        

 

   ብሉይ ኪዳን     አዲስ ኪዳን 
Search the Bible:   
     Multiple Bible Versions          62 Day Bible Reading          31 Day Bible Reading      Show Selected Verses       Select All Verses      Clear Selected Verses       Clear Screen     Font Size:       Alignment:  
1. በምድርም ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ራብ በላይ ራብ ሆነ፤ ይስሐቅም ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቢሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ።
2. እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው። ወደ ግብፅ አትውረድ፥ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ እንጂ።
3. በዚህች ምድር ተቀመጥ፥ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፥ እባርክሃለሁም፤ እነዚህን ምድሮች ሁሉ ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህ ለአብርሃም የማልሁለትንም መሐላ አጸናለሁ።
4. ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ እነዚህንም ምድሮች ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም አህዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤
5. አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን ሕጌንም ጠብቆአልና።
6. ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ።
7. የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ጠየቁት፤ እርሱም። እኅቴ ናት አለ፤ የዚህ ስፍራ ስዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፤ እርስዋ ውብ ነበረችና።
8. በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ በመስኮት ሆኖ ጎበኘ፥ ይስሐቅም ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ።
9. አቢሜሌክም ይስሐቅን ጠራ፥ እንዲህም አለው። እነሆ ሚስትህ ናት፤ እንዴትስ እርስዋን። እኅቴ ናት አልህ? ይስሐቅም። በእርስዋ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው አለው።
10. አቢሜሌክም አለ። ይህ ያደረግህብን ምንድር ነው? ከሕዝብ አንዱ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፥ ኃጢአትንም ልታመጣብን ነበር።
11. አቢሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ። ይህን ሰው ሚስቱንም የሚነካ ሞትን ይሙት ብሎ አዘዘ።
12. ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፥ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ አገኘ፤ እግዚአብሔርም ባረከው።
13. ባለ ጠጋ ሰውም ሆነ፥ እጅግ እስኪበልጥ ድረስም እየጨመረ ይበዛ ነበር፤
14. የበግና የላም ከብትም ሎሌዎችም እጅግ በዙለት፤ የፍልስጥኤም ሰዎች ቀኑበት።
15. በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጕድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው አፈርንም ሞሉባቸው።
16. አቢሜሌክም ይስሐቅን። ከእኛ ተለይተህ ሂድ፥ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና አለው።
17. ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፥ በጌራራም ሸለቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ።
18. ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ዘመን ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጕድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፤ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበሩና፤ አባቱም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው።
19. የይስሐቅ ሎሌዎችም በሸለቆው ውስጥ ቈፈሩ፥ በዚያም የሚመነጭ የውኃ ጕድጓድ አገኙ።
20. የጌራራ አገር እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር። ውኃው የእኛ ነው ሲሉ ተከራከሩ፤ የዚያችንም ጕድጓድ ስም ኤሴቅ ብሎ ጠራት፥ ለእርስዋ ሲሉ ተጣልተዋልና።
21. ሌላ ጕድጓድም ማሱ፥ ስለ እርስዋም ደግሞ ተጣሉ፤ ስምዋንም ስጥና ብሎ ጠራት ።
22. ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ አስቈፈረ፥ ስለ እርስዋም አልተጣሉም፤ ስምዋንም ርኆቦት ብሎ ጠራት እንዲህ ሲል። አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፥ በምድርም እንበዛለን።
23-24. ከዚያም ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፥ እንዲህም አለው። እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ አትፍራ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ ባሪያዬ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛለሁ።
25. በዚያም መሠዊያን ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፥ በዚያም ድንኳን ተከለ፤ የይስሐቅም ሎሌዎች በዚያ ጕድጓድ ማሱ።
26. አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱም አለቃ ፊኮል ከጌራራ ወደ እርሱ ሄዱ።
27. ይስሐቅም። ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? እናንተ ጠልታችሁኛል፥ ከእናንተም ለይታችሁ አሳድዳችሁኛል አላቸው።
28-29. እነርሱም አሉት። እግዚአብሔር ከአንተ ጋር እንዳለ በእርግጥ አየን፤ ስለዚህም። በእኛና በአንተ መካከል መሐላ ይሁን፤ እኛ አንተን እንዳልነካንህ፥ በጎነትንም ብቻ እንዳሳየንህ፥ በደኅናም እንደ ሰደድንህ፥ አንተም ክፉ እንዳትሠራብን ቃል ኪዳን ከአንተ ጋር እናድርግ አልን፤ አንተ አሁን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተባረክህ ነህ።
30. ይስሐቅም ማዕድ አቀረበላቸው፥ በሉም ጠጡም።
31. ማልደውም ተነሡ፥ እርስ በርሳቸውም ተማማሉ፤ ይስሐቅም አሰናበታቸው፥ ከእርሱም ወጥተው በደኅና ሄዱ።
32. በዚያም ቀን የይስሐቅ ሎሌዎች መጡ፥ ስለቈፈሩአትም ጕድጓድ። ውኃ አገኘን ብለው ነገሩት።
33. ስምዋንም ሳቤህ ብሎ ጠራት፤ ስለዚህም የከተማይቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ነው።
34. ዔሳውም አርባ ዓመት ሲሆነው የኬጢያዊ የብኤሪን ልጅ ዮዲትን፥ የኬጢያዊ የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትንም ሚስቶች አድርጎ አገባ፤
35. እነርሱም የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር።
Background Pictures
 Go Back