Chap.   
☐ 1. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
☐ 2. ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።
☐ 3. እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።
☐ 4. እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።
☐ 5. እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።
☐ 6. እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።
☐ 7. እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 8. እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።
☐ 9. እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ።
☐ 10. እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 11. እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 12. ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 13. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።
☐ 14. እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤
☐ 15. በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 16. እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
☐ 17. እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤
☐ 18. በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 19. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።
☐ 20. እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።
☐ 21. እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☑ 22. እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።
  ዘፍ 8:17  ከአንተ ጋር ያሉትን አራዊት ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ፥ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር አውጣቸው፤ በምድር ላይ ይርመስመሱ፥ ይዋለዱ፥ በምድርም ላይ ይብዙ።
  ዘፍ 9:1  እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው። ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት።
  ዘፍ 35:11  እግዚአብሔርም አለው። ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ።
  ዘፍ 30:30  ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፤ ወደ አንተ በመምጣቴም እግዚአብሔር ባረክህ፤ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?
  ዘፍ 1:28  እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
  ዘፍ 30:27  ላባም። በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው።
  ዘሌ 26:9  ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ።
  ኢዮ 40:15  ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል።
  ኢዮ 42:12  እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፤ አሥራ አራት ሺህም በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት።
  መዝ 107:38  ባረካቸውም እጅግም በዙ፤ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም።
  መዝ 107:31  ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ።
  መዝ 144:13-14  ዕቃ ቤቶቻቸውም የተሞሉ በየዓይነቱ ዕቃ የሚሰጡ፥ በጎቻቸውም ብዙ የሚወልዱ፥ በማሰማርያቸውም የሚበዙ፥  ላሞቻቸውም የሚሰቡ፤ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ የሌለው፥ በአደባባዮቻቸውም ዋይታ የሌለ፤
  መዝ 128:3  ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው።
  ምሳ 10:22  የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፥ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።
☐ 23. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን።
☐ 24. እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 25. እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 26. እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።
☐ 27. እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
☐ 28. እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
☐ 29. እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤
☐ 30. ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 31. እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።
 
  
  Chap.