Chap.   
የፍጥረት አጀማመር
☐ 1. በመጀመሪያ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።
☐ 2. ምድርም ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች።[1] የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር። የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መንፈስ በውሆች ላይ ይረብብ ነበር።
☐ 3. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ።
☐ 4. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑ መልካም እንደሆነ አየ፤ ብርሃኑን ከጨለማ ለየ።
☐ 5. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ብርሃኑን “ቀን”፣ ጨለማውን “ሌሊት” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን።
☐ 6. እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሃን ከውሃ የሚለይ ጠፈር በውሆች መካከል ይሁን” አለ።
☐ 7. ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን አድርጎ ከጠፈሩ በላይና ከጠፈሩ በታች ያለውን ውሃ ለየ፤ እንዳለውም ሆነ።
☐ 8. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። መሸ፤ ነጋም፤ ሁለተኛ ቀን።
☐ 9. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ከሰማይ በታች ያለው ውሃ በአንድ ስፍራ ይከማች፤ ደረቁ ምድር ይገለጥ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ።
☐ 10. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ደረቁን ምድር፣ “የብስ”፣ በአንድነት የተሰበሰበውን ውሃ፣ “ባሕር” ብሎ ጠራው። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
☐ 11. እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ዕፀዋትንም፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በምድር ላይ ዘር ያዘሉ ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን እንደየወገናቸው ታብቅል” አለ፤ እንዳለውም ሆነ።
☐ 12. ምድር ዕፀዋትን፣ እንደየወገናቸው ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና በውስጣቸው ዘር ያለባቸው ፍሬ የሚያፈሩትን ዛፎች በየወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
☐ 13. መሸ፤ ነጋም፤ ሦስተኛ ቀን።
☐ 14. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት ወቅቶች፣ ቀናትና ዓመታት የሚጀምሩበትንም እንዲያመለክቱ፣
☐ 15. ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ።
☐ 16. እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ ለምድር ብርሃን ይሰጡ ዘንድ ሁለት ታላላቅ ብርሃናት አደረገ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፣ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲሠለጥን አደረገ። እንዲሁም ከዋክብትን አደረገ።
☐ 17. ለምድር ብርሃን እንዲሰጡ እነዚህን በሰማይ ጠፈር አኖራቸው።
☐ 18. ይኸውም በቀንና በሌሊት እንዲሠለጥኑ፣ ብርሃንን ከጨለማ እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
☐ 19. መሸ፤ ነጋም፣ አራተኛ ቀን።
☐ 20. እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ውሆች ሕይወት ባላቸው በሕያዋን ፍጡራን ይሞሉ፤ ወፎች ከምድር በላይ በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ።
☐ 21. በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ታላላቅ ፍጡራንን፣ በውሃ ውስጥ የሚርመሰመሱ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እንደየወገናቸው እንዲሁም ክንፍ ያላቸውን ወፎች ሁሉ እንደየወገናቸው ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
☐ 22. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው።
☐ 23. መሸ፤ ነጋም፤ አምስተኛ ቀን።
☐ 24. እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ምድር ሕያዋን ፍጡራንን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንንና የዱር እንስሳትን እያንዳንዱን እንደ ወገኑ ታስገኝ” አለ፤ እንዳለውም ሆነ።
☐ 25. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
☐ 26. እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር[2] ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።
☐ 27. ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
☑ 28. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው።
  ዘፍ 9:7  እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሠራፋ።”
  ዘሌ 26:9  “ ‘ፊቴን ወደ እናንተ እመልሳለሁ፤ እንድታፈሩና እንድትበዙም አደርጋችኋለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ።
  ዘፍ 17:20  ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ።
  ዘፍ 22:17-18  በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤  ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”
  ዘፍ 9:1  እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤
  መዝ 128:3-4  ሚስትህ በቤትህ፣ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ወንዶች ልጆችህ በማእድህ ዙሪያ፣ እንደ ወይራ ተክል ናቸው።  እነሆ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው፣ እንዲህ ይባረካል።
  ዘፍ 26:24  በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው።
  1ዜና 4:10  ያቤጽም፣ “አቤቱ፤ እንድትባርከኝ፣ ግዛቴንም እንድታሰፋልኝ እለምንሃለሁ፤ እጅህ ከእኔ ጋር ትሁን፤ ከሥቃይና ከጒዳትም ጠብቀኝ” በማለት ወደ እስራኤል አምላክ ጮኸ። እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው።
  ዘፍ 17:16  እኔ እባርካታለሁ ከእርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።”
  1ጢሞ 4:3  እነርሱ፣ ሰዎች እንዳያገቡ ይከለክላሉ፤ የሚያምኑና እውነትን የሚያውቁ ሰዎች እግዚአብሔር የፈጠረውን በምስጋናም የሚቀበሉትን እንዳይበሉ ያዛሉ፤
  ዘፍ 1:22  እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ የባሕርንም ውሃ ሙሏት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው።
  መዝ 127:1-5  የሰሎሞን መዝሙረ መዓርግ እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፣ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል።  የዕለት ጒርስ ለማግኘት በመጣር፣ ማልዳችሁ መነሣታችሁ፣ አምሽታችሁም መተኛታችሁ ከንቱ ነው፤ እርሱ ለሚወዳቸው እንቅልፍን ያድላልና።[158]  እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው።  በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው።  ኰረጆዎቹ በእነዚህ የተሞሉ፣ የተባረከ ሰው ነው፤ ከጠላቶቻቸው ጋር በአደባባይ በሚሟገቱበት ጊዜ፣ አይዋረዱም።
  ኢዮ 42:12  እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ። እርሱም ዐሥራ አራት ሺህ በጎች፣ ስድስት ሺህ ግመሎች፣ አንድ ሺህ ጥማድ በሬዎች፣ አንድ ሺህ እንስት አህዮችም ነበሩት።
  1ዜና 26:5  ስድስተኛው ዓሚኤል፣ ሰባተኛው ይሳኮር፣ ስምንተኛው ፒላቲ፤ እግዚአብሔር ዖቤድኤዶምን ባርኮታልና።
  ዘፍ 24:60  ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤ “እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”።
  መዝ 107:38  ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤ የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም።
  ዘፍ 33:5  ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን አየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው።
  ዘፍ 49:25  አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣[187] ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።
  ዘፍ 26:3-4  ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ።  ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ፤
  ኢሳ 45:18  ሰማያትን የፈጠረ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
  ዘፍ 8:17  እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋር ያሉትን እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”
  መዝ 69:34  ሰማይና ምድር፣ ባሕርም፣ በውስጣቸውም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመስግኑት።
☐ 29. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ።
☐ 30. እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ።
☐ 31. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።
 
  
  Chap.