Chap.   
☐ 1. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
☐ 2. ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።
☐ 3. እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።
☐ 4. እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።
☐ 5. እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።
☐ 6. እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።
☐ 7. እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 8. እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።
☐ 9. እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ።
☐ 10. እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 11. እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 12. ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 13. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።
☐ 14. እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤
☐ 15. በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 16. እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
☐ 17. እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤
☐ 18. በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 19. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።
☐ 20. እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።
☐ 21. እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 22. እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።
☐ 23. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን።
☐ 24. እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 25. እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 26. እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።
☐ 27. እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
☐ 28. እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
☑ 29. እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤
  መዝ 147:9  ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል።
  መዝ 115:16  የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።
  መዝ 24:1  ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ።
  ዘፍ 2:16  እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤
  ሐዋ 17:28  ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ። እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።
  መዝ 104:14-15  እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፥ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል።  ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ያበራል፥ እህልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል።
  ሆሴ 2:8  ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፥ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ።
  ሐዋ 17:24-25  ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤  እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።
  1ኛ ጢሞ 6:17  በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
  ማቴ 6:25-26  ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?  ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?
  ኢዮ 36:31  በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ብዙም ምግብ ይሰጣል።
  ኢሳ 33:16  እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።
  መዝ 136:25  ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
  መዝ 111:5  ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።
  ማቴ 6:11  የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤
  መዝ 146:7  ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል፤
  ሐዋ 14:17  ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።
  መዝ 145:15-16  የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ።  አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።
  መዝ 104:27-28  ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።  በሰጠሃቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ፤ እጅህን ትከፍታለህ፥ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ።
  ዘፍ 9:3  ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ።
☐ 30. ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 31. እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።
 
  
  Chap.