Chap.   
☐ 1. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
☐ 2. ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።
☐ 3. እግዚአብሔርም። ብርሃን ይሁን ኣለ፤ ብርሃንም ሆነ።
☐ 4. እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ሆነ አየ፤ እግዚብሔርም ብርሃንንና ጨለማን ለየ።
☐ 5. እግዚአብሔርም ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፥ ጨለማውንም ሌሊት አለው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አንድ ቀን።
☐ 6. እግዚአብሔርም። በውኆች መካከል ጠፈር ይሁን፥ በውኃና በውኃ መካከልም ይክፈል አለ።
☐ 7. እግዚአብሔርም ጠፈርን አደረገ፥ ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉትንም ውኆች ለየ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 8. እግዚአብሔር ጠፈርን ሰማይ ብሎ ጠራው። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሁለተኛ ቀን።
☑ 9. እግዚአብሔርም። ከሰማይ በታች ያለው ውኃ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ፥ የብሱም ይገለጥ አለ እንዲሁም ሆነ።
  መዝ 95:5  ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት።
  መዝ 24:1-2  ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ።  እርሱ በባሕሮች መሥርቶአታልና፥ በፈሳሾችም አጽንቶአታልና።
  መዝ 33:7  የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው።
  2ኛ ጴጥ 3:5  ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤
  መክ 1:7  ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ።
  ምሳ 8:28-29  ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥  ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥
  ኢዮ 38:8-11  ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው?  ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፤  ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ።  እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፤ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ።
  መዝ 136:5-6  ሰማያትን በብልሃት የሠራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤  ምድርን በውኃ ላይ ያጸና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤
  ኤር 5:22  በውኑ እኔን አትፈሩምን? ከፊቴስ አትደነግጡምን? ይላል እግዚአብሔር፤ እንዳያልፍ አሸዋን በዘላለም ትእዛዝ ለባሕር ዳርቻ አድርጌአለሁ፤ ሞገዱም ቢናወጥ አያሸንፍም፥ ቢጮኽም አያልፍበትም።
  መዝ 104:3  እልፍኙን በውኃ የሚሠራ፥ ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ፥ በነፋስ ክንፍም የሚሄድ፥
  ኢዮ 26:10  ብርሃንና ጨለማ እስከሚለያዩበት ዳርቻ ድረስ፥ በውኆች ፊት ላይ ድንበርን አደረገ።
  መዝ 104:5-9  ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት።  በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንሃት፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ።  ከዘለፋህም ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ ይደነግጣሉ፤  ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ቈላዎች ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ ይወርዳሉ፤  እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ።
  ራእ 10:6  ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ።
  ዮና 1:9  እርሱም። እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ በሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን እመልካለሁ አላቸው።
  ኢዮ 26:7  ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል።
☐ 10. እግዚአብሔርም የብሱን ምድር ብሎ ጠራው፤ የውኃ መከማቻውንም ባሕር አለው፤ እግዚእብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 11. እግዚአብሔርም። ምድር ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘሩ ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል አለ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 12. ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 13. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ሦስተኛ ቀን።
☐ 14. እግዚአብሔርም አለ። ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤
☐ 15. በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 16. እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ።
☐ 17. እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው፤
☐ 18. በቀንም በሌሊትም እንዲሠለጥኑ፥ ብርሃንንና ጨለማንም እንዲለዩ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 19. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አራተኛ ቀን።
☐ 20. እግዚአብሔርም አለ። ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፥ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ።
☐ 21. እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፥ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 22. እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ባረካቸው። ብዙ ተባዙም የባሕርንም ውኃ ሙሉአት፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ።
☐ 23. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ አምስተኛ ቀን።
☐ 24. እግዚአብሔርም አለ። ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 25. እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፥ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፥ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ፤ እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ።
☐ 26. እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።
☐ 27. እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
☐ 28. እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።
☐ 29. እግዚአብሔርም አለ። እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ፤
☐ 30. ለምድርም አራዊት ሁሉ፥ ለሰማይም ወፎች ሁሉ፥ ሕያው ነፍስ ላላቸው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላቸው፤ እንዲሁም ሆነ።
☐ 31. እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን።
 
  
  Chap.